የዮሐንስ ራእይ 16
Amharic NT

1ለሰባቱም መላእክት። ሄዳችሁ የእግዚአብሔርን ቁጣ ጽዋዎች በምድር ውስጥ አፍስሱ የሚል ታላቅ ድምፅ ከመቅደሱ ሰማሁ።

2ፊተኛውም ሄዶ ጽዋውን በምድር ውስጥ አፈሰሰ፤ የአውሬውም ምልክት ባለባቸው ለምስሉም በሚሰግዱ ሰዎች ክፉኛ የሚነዘንዝ ቍስል ሆነባቸው።

3ሁለተኛውም ጽዋውን በባሕር ውስጥ አፈሰሰ፤ እንደ ሞተም ሰው ደም ሆነ፥ በባሕርም ከሚኖሩት ሕይወት ያለበት ነፍስ ሁሉ ሞተ።

4ሦስተኛውም ጽዋውን በወንዞችና በውኃ ምንጮች ውስጥ አፈሰሰ፤ እነርሱም ደም ሆኑ። 5የውኃውም መልአክ። ያለህና የነበርህ ጌታ ሆይ፥ ቅዱስ ሆይ፥ እንዲህ ስለፈረድህ ጻድቅ ነህ፤ 6የቅዱሳንና የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ ደምን ደግሞ አጠጥተሃቸዋል፥ የሚገባቸው ነውና ብሎ ሲናገር ሰማሁ። 7ከመሰዊያውም። አዎን፥ ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፥ ፍርዶችህ እውነትና ጽድቅ ናቸው ብሎ ሲናገር ሰማሁ።

8አራተኛውም ጽዋውን በፀሐይ ላይ አፈሰሰ፤ ሰዎችንም በእሳት ልታቃጥል ተሰጣት። 9ሰዎችም በታላቅ ትኵሳት ተቃጠሉ፥ በነዚህም መቅሠፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ፥ ክብርንም እንዲሰጡት ንስሐ አልገቡም።

10አምስተኛውም ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ፤ መንግሥቱም ጨለማ ሆነች ከስቃይም የተነሳ መላሶቻቸውን ያኝኩ ነበር፥ 11ከስቃያቸውና ከቍስላቸውም የተነሳ የሰማይን አምላክ ተሳደቡ፥ ከስራቸውም ንስሐ አልገቡም።

12ስድስተኛውም ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከፀሐይም መውጫ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲሰናዳላቸው ውኃው ደረቀ።

13ከዘንዶውም አፍና ከአውሬው አፍ ከሐሰተኛውም ነቢይ አፍ ጓጕንቸሮች የሚመስሉ ሦስት ርኵሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ፤ 14ምልክት እያደረጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸውና፥ በታላቁም ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሔር ቀን ወደ ሚሆነው ጦር እንዲያስከትቱአቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይወጣሉ። 15እነሆ፥ እንደ ሌባ ሆኜ እመጣለሁ፤ ራቁቱን እንዳይሄድ እፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው። 16በዕብራይስጥም አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ እስከተቱአቸው።

17ሰባተኛውም ጽዋውን በአየር ውስጥ አፈሰሰ፤ ከመቅደሱም ውስጥ። ተፈጽሞአል የሚል ታላቅ ድምጽ ከዙፋኑ ወጣ። 18መብረቅና ድምጽም ነጎድጓድም ሆኑ፥ ትልቅም የምድር መናወጥ ሆነ፤ ሰው በምድር ከተፈጠረ ጀምሮ እንዲህ ያለ ታላቅ መናውጥ ከቶ አልነበረም፤ ከሁሉ በለጠ። 19ታላቂቱም ከተማ በሦስት ተከፋፈለች፥ የአሕዛብም ከተማዎች ወደቁ። ታላቂቱም ባቢሎን የብርቱ ቍጣው ወይን ጠጅ የሞላበትን ጽዋ እንዲሰጣት በእግዚአብሔር ፊት ታሰበች። 20ደሴቶችም ሁሉ ሸሹ ተራራዎችም አልተገኙም። 21በሚዛንም አንድ ታላንት*ፍ1* የሚያህል ታላቅ በረዶ በሰዎች ላይ ከሰማይ ወረደባቸው፤ ሰዎቹም ከበረዶው መቅሰፍት የተነሳ እግዚአብሔርን ተሳደቡ፥ መቅሰፍቱ እጅግ ታላቅ ነውና።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Revelation 15
Top of Page
Top of Page