1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5
Amharic NT

1እንግዲህ እኔ፥ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ የክርስቶስም መከራ ምስክር ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ፥ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤ 2በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ 3ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤ 4የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ።

5እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።

6እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ 7እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 8በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ 9በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።

10በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁምል ያበረታችሁማል። 11ለእርሱ ክብርና ኃይል እስከዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን።

12እየመከርኋችሁና የምትቆሙባት ጸጋ እውነትኛ የእግዚአብሔር ጸጋ እንድትሆን እየመሰከርሁላችሁ፥ የታመነ ወንድም እንደ ሆነ በቈጠርሁት በስልዋኖስ እጅ በአጭሩ ጽፌላችኋለሁ። 13ከእናንተ ጋር ተመርጣ በባቢሎን ያለች ቤተ ክርስቲያን ልጄም ማርቆስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 14በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁ ሰላም ይሁን። አሜን።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

1 Peter 4
Top of Page
Top of Page