የዮሐንስ ራእይ 9
Amharic NT

1አምስተኛውም መልአክ ነፋ፤ ከሰማይም ወደ ምድር ወድቆ የነበረ ኮከብ አየሁ፥ የጥልቁም ጕድጓድ መክፈቻ ተሰጠው። 2የጥልቁንም ጕድጓድ ከፈተው፤ ጢስም ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ጢስ ሆኖ ከጕድጓዱ ወጣ ፀሐይና አየርም በጕድጓዱ ጢስ ጨለሙ። 3ከጢሱም አንበጣዎች ወደ ምድር ወጡ፥ የምድርም ጊንጦች ሥልጣን እንዳላቸው ሥልጣን ተሰጣቸው። 4የእግዚአብሔርም ማኅተም በግምባራቸው ከሌለባቸው ሰዎች በቀር በምድር ያለውን ሣር ቢሆንም ወይም ማናቸውንም የለመለመ ነገር ወይም ማናቸውንም ዛፍ እንዳይጐዱ ተባለላቸው። 5አምስትም ወር ሊሣቅዩአቸው ተሰጣቸው እንጂ ሊገድሉአቸው አይደለም፤ እነርሱም የሚሣቅዩት ሥቃይ ጊንጥ ሰውን ነድፎ እንደሚሣቅይ ነው። 6በዚያም ወራት ሰዎች ሞትን ይፈልጋሉ አያገኙትምም፥ ሊሞቱም ይመኛሉ ሞትም ከእነርሱ ይሸሻል።

7የአንበጣዎቹም መልክ ለጦርነት እንደ ተዘጋጁ ፈረሶች ነው፥ በራሳቸውም ላይ ወርቅ እንደሚመስሉ አክሊሎች ነበሩአቸው፥ ፊታቸውም እንደ ሰው ፊት ነበረ፤ 8የሴቶችን ጠጕር የሚመስል ጠጕር ነበራቸው፥ ጥርሳቸውም እንደ አንበሳ ጥርስ ነበረ፥ 9የብረት ጥሩር የሚመስልም ጥሩር ነበራቸው፥ የክንፋቸውም ድምፅ ወደ ጦርነት እንደሚጋልቡ እንደ ብዙ ፈረሶች ሰረገላዎች ድምፅ ነበረ። 10እንደ ጊንጥም ጅራት ያለ ጅራት አላቸው በጅራታቸውም መውጊያ አለ፥ ሰዎችንም አምስት ወር እንዲጐዱ ሥልጣን አላቸው። 11በእነርሱም ላይ ንጉሥ አላቸው እርሱም የጥልቅ መልአክ ነው፥ ስሙም በዕብራይስጥ አብዶን በግሪክም አጶልዮን ይባላል።

12ፊተኛው ወዮ አልፎአል፤ እነሆ፥ ከዚህ በኋላ ገና ሁለት ወዮ ይመጣል።

13ስድስተኛውም መልአክ ነፋ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ካለ በወርቅ ከተሠራ መሠዊያ ቀንዶች አንድ ድምፅ ሰማሁ፥ 14መለከትም ያለውን ስድስተኛውን መልአክ። በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው አለው። 15የሰዎችንም ሲሶ እንዲገድሉ ለሰዓቱና ለቀኑ ለወሩም ለዓመቱም ተዘጋጅተው የነበሩ አራቱ መላእክት ተፈቱ። 16የፈረሰኞችም ጭፍራ ቁጥር እልፍ ጊዜ እልፍ፥ እልፍ ጊዜ እልፍ ነበረ፤ ቁጥራቸውን ሰማሁ። 17ፈረሶቹንና በእነርሱም ላይ የተቀመጡትን እንዲሁ በራእይ አየሁ፤ እሳትና ያክንት ዲንም የሚመስል ጥሩር ነበራቸው፤ የፈረሶቹም ራስ እንደ አንበሳ ራስ ነበረ፥ ከአፋቸውም እሳትና ጢስ ዲንም ወጣ። 18ከአፋቸውም በወጡት በእሳቱና በጢሱ በዲኑም በእነዚህ ሦስት መቅሰፍቶች የሰዎቹ ሲሶ ተገደለ። 19የፈረሶቹ ሥልጣን በአፋቸውና በጅራታቸው ነውና፤ ጅራታቸው እባብን ይመስላልና፥ ራስም አላቸው በእርሱም ይጐዳሉ።

20በእነዚህም መቅሠፍቶች ያልተገደሉት የቀሩቱ ሰዎች ለአጋንንትና ያዩ ወይም ይሰሙ ወይም ይሄዱ ዘንድ ለማይችሉ ከወርቅና ከብር ከናስም ከድንጋይም ከእንጨትም ለተሠሩ ለጣዖቶች እንዳይሰግዱ ስለ እጃቸው ሥራ ንስሐ አልገቡም፤ 21ስለ መግደላቸውም ቢሆን ወይም ስለ አስማታቸው ወይም ስለ ዝሙታቸው ወይም ስለ ስርቆታቸው ንስሐ አልገቡም።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Revelation 8
Top of Page
Top of Page