1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1
Amharic NT

1የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ጴጥሮስ፥ እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ እንዳወቃቸው በመንፈስም እንደሚቀደሱ፥ ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ ለተመረጡት በጳንጦስና በገላትያ በቀጰዶቅያም በእስያም በቢታንያም ለተበተኑ መጻተኞች፤ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2

3ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል። 4 5 6በዚህም እጅግ ደስ ይላችኋል፥ ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል። 7 8እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ አምናችሁ፥ የእምነታችሁን ፍፃሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ፥ በማይነገርና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ይላችኋል። 9

10ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው እየፈለጉ መረመሩት፤ 11በእነርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ፥ ስለ ክርስቶስ መከራ ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ እየመሰከረ፥ በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር። 12ለእነርሱም ከሰማይ በተላከ በመንፈስ ቅዱስ ወንጌልን የሰበኩላችሁ ሰዎች አሁን ባወሩላችሁ ነገር እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው፤ ይህንም ነገር መላእክቱ ሊመለከቱ ይመኛሉ።

13ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ። 14እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ። 15ዳሩ ግን። እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ። 16

17ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ ብትጠሩ በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃት ኑሩ። 18ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። 19 20ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፥ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ። 21

22ለእውነት እየታዘዛችሁ ግብዝነት ለሌለበት ለወንድማማች መዋደደ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ እርስ በርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። 23ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ።

24ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና፤ ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል፤

25የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል። በወንጌልም የተሰበከላችሁ ቃል ይህ ነው።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

James 5
Top of Page
Top of Page