የሐዋርያት ሥራ 7
Amharic NT

1ሊቀ ካህናቱም። ይህ ነገር እንዲህ ነውን? አለው፤

2እርሱም እንዲህ አለ። ወንድሞችና አባቶች ሆይ፥ ስሙ። የክብር አምላክ ለአባታችን ለአብርሃም በካራን ሳይቀመጥ ገና በሁለት ወንዝ መካከል ሳለ ታየና። 3ከአገርህና ከዘመዶችህም ወጥተህ ወደማሳይህ ወደ ማንኛውም ምድር ና አለው። 4በዚያን ጊዜ ከከለዳውያን አገር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ። ከዚያም አባቱ ከሞተ በኋላ እናንተ ዛሬ ወደምትኖሩባት ወደዚች አገር አወጣው። 5በዚችም የእግር ጫማ ስንኳ የሚያህል ርስት አልሰጠውም፤ ነገር ግን ልጅ ሳይኖረው ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ርስት አድርጎ ይሰጠው ዘንድ ተስፋ ሰጠው። 6እግዚአብሔርም ዘሩ በሌላ አገር መጻተኞች እንዲሆኑ አራት መቶ ዓመትም ባሪያዎች እንዲያደርጉአቸው እንዲያስጨንቁአቸውም እንዲህ ተናገረ፤ 7ደግሞም እግዚአብሔር። እንደ ባሪያዎች በሚገዙአቸው ሕዝብ ላይ እኔ እፈርድባቸዋለሁ፥ ከዚህም በኋላ ይወጣሉ በዚህም ስፍራ ያመልኩኛል አለ። 8የመገረዝንም ኪዳን ሰጠው፤ እንዲሁም ይስሐቅን ወለደ በስምንተኛውም ቀን ገረዘው ይስሐቅም ያዕቆብን ያዕቆብም አሥራ ሁለቱን የአባቶችን አለቆች።

9የአባቶችም አለቆች በዮሴፍ ቀንተው ወደ ግብፅ ሸጡት፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፥ 10ከመከራውም ሁሉ አወጣው፥ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖንም ፊት ሞገስንና ጥበብን ሰጠው፥ በግብፅና በቤቱ ሁሉ ላይም ቢትወደድ አድርጎ ሾመው።

11በግብፅና በከነዓንም አገር ሁሉ ራብና ብዙ ጭንቅ መጣ፥ አባቶቻችንም ምግብን አላገኙም። 12ያዕቆብም በግብፅ እህል መኖሩን በሰማ ጊዜ በመጀመሪያ አባቶቻችንን ሰደዳቸው፤ 13በሁለተኛውም ዮሴፍ ለወንድሞቹ ታወቀ፥ የዮሴፍም ትውልድ በፈርዖን ዘንድ ተገለጠ። 14ዮሴፍም አባቱን ያዕቆብንና ሰባ አምስት ነፍስ የነበረውን ቤተ ዘመድ ሁሉ ልኮ አስጠራ። 15ያዕቆብም ወደ ግብፅ ወረደ እርሱም ሞተ አባቶቻችንም፤ 16ወደ ሴኬምም አፍልሰው አብርሃም ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በብር በገዛው መቃብር ቀበሩአቸው።

17እግዚአብሔርም ለአብርሃም የማለለት የተስፋው ዘመን ሲቀርብ፥ ዮሴፍን የማያውቀው ሌላ ንጉሥ በግብፅ ላይ እስኪነሣ ድረስ፥ ሕዝቡ እየተጨመሩ በግብፅ በዙ። 18 19እርሱም ወገናችንን ተተንኵሎ ሕፃናትን በሕይወት እንዳይጠብቁ ወደ ውጭ ይጥሉ ዘንድ አድርጎ አባቶቻችንን አስጨነቀ። 20በዚያን ጊዜ ሙሴ ተወለደ በእግዚአብሔርም ፊት ያማረ ነበር፤ በአባቱ ቤትም ሦስት ወር አደገ፤ 21በተጣለም ጊዜ የፈርዖን ልጅ አነሣችው ልጅም ይሆናት ዘንድ አሳደገችው። 22ሙሴም የግብፆችን ጥበብ ሁሉ ተማረ፥ በቃሉና በሥራውም የበረታ ሆነ። 23ነገር ግን አርባ ዓመት ሲሞላው ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ይጐበኝ ዘንድ በልቡ አሰበ። 24አንዱም ሲበደል አይቶ ረዳው፥ የግብፅን ሰውም መትቶ ለተገፋው ተበቀለ። 25ወንድሞቹም እግዚአብሔር በእጁ መዳንን እንዲሰጣቸው የሚያስተውሉ ይመስለው ነበር፥ እነርሱ ግን አላስተዋሉም። 26በማግሥቱም እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አገኛቸው፥ ሊያስታርቃቸውም ወዶ። ሰዎች ሆይ፥ እናንተስ ወንድማማች ናችሁ፤ ስለ ምን እርስ በርሳችሁ ትበዳደላላችሁ? አላቸው። 27ያም ባልንጀራውን የሚበድል ግን። አንተን በእኛ ላይ ሹምና ፈራጅ እንድትሆን የሾመህ ማን ነው? 28ወይስ ትናንትና የግብፁን ሰው እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትወዳለህን? ብሎ ገፋው። 29ሙሴም ከዚህ ነገር የተነሣ ሸሽቶ በምድያም አገር መጻተኛ ሆኖ ኖረ፤ በዚያም ሁለት ልጆች ወለደ።

30አርባ ዓመትም ሲሞላ የጌታ መልአክ በሲና ተራራ ምድረ በዳ በቍጥቋጦ መካከል በእሳት ነበልባል ታየው። 31ሙሴም አይቶ ባየው ተደነቀ፤ ሊመለከትም ሲቀርብ የጌታ ቃል። እኔ የአባቶችህ አምላክ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ ብሎ ወደ እርሱ መጣ። ሙሴም ተንቀጥቅጦ ሊመለከት አልደፈረም። 32 33ጌታም። የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች ምድር ናትና የእግርህን ጫማ አውልቅ። 34በግብፅ ያሉትን የሕዝቤን መከራ ፈጽሜ አይቼ መቃተታቸውንም ሰምቼ ላድናቸው ወረድሁ፤ አሁንም ና፥ ወደ ግብፅ እልክሃለሁ አለው።

35ሹምና ፈራጅ እንድትሆን የሾመህ ማን ነው? ብለው የካዱትን፥ ይህን ሙሴን በቍጥቋጦው በታየው በመልአኩ እጅ እግዚአብሔር ሹምና ቤዛ አድርጎ ላከው። 36ይህ ሰው በግብፅ ምድርና በኤርትራ ባሕር በምድረ በዳም አርባ ዓመት ድንቅና ምልክት እያደረገ አወጣቸው። 37ይህ ሰው ለእስራኤል ልጆች። እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋል፤ እርሱን ስሙት ያላቸው ሙሴ ነው። 38ይህ ሰው በሲና ተራራ ከተናገረው መልአክና ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ በማኅበሩ ውስጥ የነበረው ነው፤ ይሰጠንም ዘንድ ሕይወት ያላቸውን ቃላት ተቀበለ፤ 39ለእርሱም አባቶቻችን ሊታዘዙት አልወደዱም፤ ነገር ግን ገፉት በልባቸውም ወደ ግብፅ ተመለሱ፤ 40አሮንንም። በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና አሉት። 41በዚያም ወራት ጥጃ አደረጉ ለጣዖቱም መሥዋዕት አቀረቡ፥ በእጃቸውም ሥራ ደስ አላቸው። 42እግዚአብሔር ግን ዘወር አለ የሰማይንም ጭፍራ ያመልኩ ዘንድ አሳልፎ ሰጣቸው፥ በነቢያትም መጽሐፍ። እናንተ የእስራኤል ቤት፥ አርባ ዓመት በምድረ በዳ የታረደውን ከብትና መሥዋዕትን አቀረባችሁልኝን? 43ትሰግዱላቸውም ዘንድ የሠራችኋቸውን ምስሎች እነርሱንም የሞሎክን ድንኳንና ሬምፉም የሚሉትን የአምላካችሁን ኮከብ አነሣችሁ፤ እኔም ከባቢሎን ወዲያ እሰዳችኋለሁ ተብሎ እንዲህ ተጽፎአል።

44እንዳየው ምስል አድርጎ ይሠራት ዘንድ ሙሴን ተናግሮ እንዳዘዘው፥ የምስክር ድንኳን ከአባቶቻችን ዘንድ በምድረ በዳ ነበረች፤ 45አባቶቻችንም ደግሞ በተራ ተቀብለው እግዚአብሔር በፊታቸው ያወጣቸውን የአሕዛብን አገር በያዙት ጊዜ ከኢያሱ ጋር አገቡአት፥ እስከ ዳዊት ዘመንም ድረስ ኖረች። 46እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝቶ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያን ያገኝ ዘንድ ለመነ። 47ነገር ግን ሰሎሞን ቤት ሠራለት። 48ነገር ግን ነቢዩ። ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ ለእኔ ምን ዓይነት ቤት ትሠራላችሁ? ይላል ጌታ፥ ወይስ የማርፍበት ስፍራ ምንድር ነው? ይህንስ ሁሉ እጄ የሠራችው አይደለምን? እንዳለ፥ ልዑል የሰው እጅ በሠራችው አይኖርም።

49

50

51እናንተ አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሮአችሁም ያልተገረዘ፥ እናንተ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ፤ አባቶቻችሁ እንደ ተቃወሙት እናንተ ደግሞ። 52ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ገደላችሁትም። 53

54ይህንም በሰሙ ጊዜ በልባቸው በጣም ተቈጡ ጥርሳቸውንም አፋጩበት። 55መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና። 56እነሆ፥ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ። 57በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፈኑ፥ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ ሮጡ፥ 58ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት። ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ። 59እስጢፋኖስም። ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር። 60ተንበርክኮም። ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ አንቀላፋ። ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Acts 6
Top of Page
Top of Page