የዮሐንስ ወንጌል 13
Amharic NT

1ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው። 2እራትም ሲበሉ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው አሳብ ካገባ በኋላ፥ 3ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ፥ 4ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤

5በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ። 6ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ፤ እርሱም። ጌታ ሆይ፥ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን? አለው። 7ኢየሱስም መልሶ። እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፥ በኋላ ግን ታስተውለዋለህ አለው። 8ጴጥሮስም። የእኔን እግር ለዘላለም አታጥብም አለው። ኢየሱስም። ካላጠብሁህ፥ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም ብሎ መለሰለት። 9ስምዖን ጴጥሮስም። ጌታ ሆይ፥ እጄንና ራሴን ደግሞ እንጂ እግሬን ብቻ አይደለም አለው። 10ኢየሱስም። የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፥ ሁለንተናው ግን ንጹሕ ነው፤ እናንተም ንጹሐን ናችሁ፥ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም አለው። 11አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና፤ ስለዚህ። ሁላችሁ ንጹሐን አይደላችሁም አለው።

12እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፥ እንዲህም አላቸው። ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? 13እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ። 14እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። 15እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። 16እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም። መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም። 17ይህን ብታውቁ፥ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ።

18ስለ ሁላችሁ አልናገርም፤ እኔ የመረጥኋቸውን አውቃለሁ፤ ነገር ግን መጽሐፍ። እንጀራዬን የሚበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣብኝ ያለው ይፈጸም ዘንድ ነው። 19በሆነ ጊዜ እኔ እንደ ሆንሁ ታምኑ ዘንድ፥ ከአሁን ጀምሬ አስቀድሞ ሳይሆን እነግራችኋለሁ። 20እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ማናቸውን የምልከውን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።

21ኢየሱስ ይህን ብሎ በመንፈሱ ታወከ መስክሮም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል አለ። 22ደቀ መዛሙርቱ ስለ ማን እንደ ተናገረ አመንትተው እርስ በርሳቸው ተያዩ። 23ኢየሱስም ይወደው የነበረ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ በኢየሱስ ደረት ላይ ተጠጋ፤ 24ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ እርሱን ጠቅሶ። ስለማን እንደ ተናገረ ንገረን አለው። 25እርሱም በኢየሱስ ደረት እንዲህ ተጠግቶ። ጌታ ሆይ፥ ማን ነው? አለው። 26ኢየሱስም። እኔ ቍራሽ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው ብሎ መለሰለት። ቍራሽም አጥቅሶ ለአስቆሮቱ ለስምዖን ልጅ ለይሁዳ ሰጠው። 27ቍራሽም ከተቀበለ በኋላ ያን ጊዜ ሰይጣን ገባበት። እንግዲህ ኢየሱስ። የምታደርገውን ቶሎ ብለህ አድርግ አለው። 28ነገር ግን ከተቀመጡት ስለ ምን ይህን እንዳለው ማንም አላወቀም፤ 29ይሁዳ ከረጢቱን የያዘ ስለ ሆነ፥ ኢየሱስ። ለበዓሉ የሚያስፈልገንን ግዛ፥ ወይም ለድሆች ምጽዋት እንዲሰጥ ያለው ለአንዳንዱ መስሎአቸው ነበርና። 30እርሱም ቍራሹን ከተቀበለ በኋላ ወዲያው ወጣ፤ ሌሊትም ነበረ።

31ከወጣም በኋላ ኢየሱስ እንዲ አለ። አሁን የሰው ልጅ ከበረ እግዚአብሔርም ሰለ እርሱ ከበረ፤ 32እግዚአብሔር ስለ እርሱ የከበረ ከሆነ፥ እግዚአብሔር ደግሞ እርሱን ራሱን ያከብረዋል ወዲያውም ያከብረዋል። 33ልጆች ሆይ፥ ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድም። እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አይቻላችሁም እንዳልኋቸው፥ አሁን ለእናንተ ደግሞ እላችኋለሁ። 34እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። 35እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።

36ስምዖን ጴጥሮስም። ጌታ ሆይ፥ ወዴት ትሄዳለህ? አለው። ኢየሱስም። ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፥ ነገር ግን በኋላ ትከተለኛለህ ብሎ መለሰለት። 37ጴጥሮስም። ጌታ ሆይ፥ አሁን ልከተልህ አለመቻሌ ስለ ምንድር ነው? ነፍሴን ስንኳ ስለ አንተ እሰጣለሁ አለው። 38ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰለት። ነፍስህን ስለ እኔ ትሰጣለህን? እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዶሮ አይጮኽም።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

John 12
Top of Page
Top of Page