የሉቃስ ወንጌል 18
Amharic NT

1ሳይታክቱም ዘወትር ሊጸልዩ እንዲገባቸው የሚል ምሳሌን ነገራቸው፥ 2እንዲህ ሲል። በአንዲት ከተማ እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰውንም የማያፍር አንድ ዳኛ ነበረ። 3በዚያችም ከተማ አንዲት መበለት ነበረች፥ ወደ እርሱም እየመጣች። ከባላጋራዬ ፍረድልኝ ትለው ነበር። 4አያሌ ቀንም አልወደደም፤ ከዚህ በኋላ ግን በልቡ። ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ ሰውንም ባላፍር፥ 5ይህች መበለት ስለምታደክመኝ ሁልጊዜም እየመጣች እንዳታውከኝ እፈርድላታለሁ አለ። 6ጌታም አለ። ዓመፀኛው ዳኛ ያለውን ስሙ። 7እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? 8እላችኋለሁ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?

9ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፥ 10እንዲህ ሲል። ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፥ አንዱ ፈሪሳዊ ሁለተኛውም ቀራጭ። 11ፈሪሳዊም ቆሞ በልቡ ይህን ሲጸልይ። እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ፤ 12በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጦማለሁ፥ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት አወጣለሁ አለ። 13ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፥ ነገር ግን። አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር። 14እላችኋለሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱን ግን የሚያዋርድ ከፍ ይላል።

15እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ደግሞ ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም አይተው ገሠጹአቸው። 16ኢየሱስ ግን ሕፃናትን ወደ እርሱ ጠርቶ። ሕፃናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉአቸው አትከልክሉአቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና። 17እውነት እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም አለ።

18ከአለቆችም አንዱ። ቸር መምህር፥ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው። 19ኢየሱስም። ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። 20ትእዛዛቱን ታውቃለህ፥ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አባትህንና እናትህን አክብር አለው። 21እርሱም። ይህን ሁሉ ከሕፃንናቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ አለ። 22ኢየሱስም ይህን ሰምቶ። አንዲት ገና ቀርታሃለች፤ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ አለው። 23እርሱ ግን ይህን ሰምቶ እጅግ ባለ ጠጋ ነበርና ብዙ አዘነ። 24ኢየሱስም ብዙ እንዳዘነ አይቶ። ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል። 25ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ሊገባ ይቀላል አለ። 26የሰሙትም። እንግዲህ ማን ሊድን ይችላል? አሉ። 27እርሱ ግን። በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል አለ።

28ጴጥሮስም። እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ አለ። 29እርሱም። እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ቤትን ወይም ወላጆችን ወይም ወንድሞችን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን የተወ፥ 30በዚህ ዘመን ብዙ እጥፍ በሚመጣውም ዓለም የዘላለምን ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም አላቸው።

31አሥራ ሁለቱንም ወደ እርሱ አቅርቦ እንዲህ አላቸው። እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ ስለ ሰው ልጅም በነቢያት የተጻፈው ሁሉ ይፈጸማል። 32ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታልና፥ ይዘብቱበትማል ያንገላቱትማል ይተፉበትማል፤ 33ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል። 34እነርሱም ከዚህ ነገር ምንም አላስተዋሉም፥ ይህም ቃል ተሰውሮባቸው ነበር፥ የተናገረውንም አላወቁም።

35ወደ ኢያሪኮም በቀረበ ጊዜ አንድ ዕውር እየለመነ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ነበር። 36ሕዝብም ሲያልፍ ሰምቶ። ይህ ምንድር ነው? ብሎ ጠየቀ። 37እነርሱም። የናዝሬቱ ኢየሱስ ያልፋል ብለው አወሩለት። 38እርሱም። የዳዊት ልጅ፥ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ እያለ ጮኸ። 39በስተ ፊት ይሄዱ የነበሩትም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን። የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ እያለ አብዝቶ ጮኸ። 40ኢየሱስም ቆሞ ወደ እርሱ እንዲያመጡት አዘዘ። በቀረበም ጊዜ። ምን ላደርግልህ ትወዳለህ? ብሎ ጠየቀው። 41እርሱም። ጌታ ሆይ፥ አይ ዘንድ ነው አለው። 42ኢየሱስም። እይ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው። 43በዚያን ጊዜም አየ፥ እግዚአብሔንም እያከበረ ተከተለው። ሕዝቡም ሁሉ አይተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Luke 17
Top of Page
Top of Page