የማርቆስ ወንጌል 3
Amharic NT

1ደግሞም ወደ ምኵራብ ገባ፥ በዚያም እጁ የሰለለች ሰው ነበር፤ 2ሊከሱትም፥ በሰንበት ይፈውሰው እንደ ሆነ ይጠባበቁት ነበር። 3እጁ የሰለለችውንም ሰው። ተነሥተህ ወደ መካከል ና አለው። 4በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን? ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳን ወይስ መግደል? አላቸው፤ እነርሱም ዝም አሉ። 5ስለ ልባቸውም ድንዛዜ አዝኖ ዙሪያውን እየተመለከተ በቍጣ አያቸው፥ ሰውየውንም። እጅህን ዘርጋ አለው። 6ዘረጋትም፥ እጁም ዳነች። ፈሪሳውያንም ወጥተው ወዲያው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ከሄሮድስ ወገን ጋር ተማከሩበት።

7ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባህር ፈቀቅ አለ፤ ከገሊላ የመጡም ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤ 8እንዴት ትልቅ ነገርም እንዳደረገው ሰምተው ብዙ ሰዎች ከይሁዳ ከኢየሩሳሌምም ከኤዶምያስም ከዮርዳኖስ ማዶም ከጢሮስና ከሲዶና ምድርም ወደ እርሱ መጡ። 9ሰዎቹም እንዳያጋፉት ታንኳን ያቆዩለት ዘንድ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው፤ 10ብዙ ሰዎችን አድኖ ነበርና፥ ስለዚህም ሥቃይ ያለባቸው ሁሉ እንዲዳስሱት ይወድቁበት ነበር። 11ርኵሳን መናፍስትም ባዩት ጊዜ በፊቱ ተደፍተው። አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ እያሉ ጮኹ። 12እንዳይገልጡትም በጣም አዘዛቸው።

13ወደ ተራራም ወጣ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፥ ወደ እርሱም ሄዱ። 14ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፥ 15ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለት አደረገ፤ 16ስምዖንንም ጴጥሮስ ብሎ ሰየመው፤ 17የዘብዴዎስንም ልጅ ያዕቆብን የያዕቆብንም ወንድም ዮሐንስን ቦአኔርጌስ ብሎ ሰየማቸው፥ የነጎድጓድ ልጆች ማለት ነው፤ 18እንድርያስንም ፊልጶስንም በርተሎሜውስንም ማቴዎስንም ቶማስንም የእልፍዮስን ልጅ ያዕቆብንም ታዴዎስንም ቀነናዊውንም ስምዖንን፥ 19አሳልፎ የሰጠውንም የአስቆሮቱን ይሁዳን።

20ወደ ቤትም መጡ፤ እንጀራም መብላት ስንኳ እስኪሳናቸው ድረስ እንደ ገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። 21ዘመዶቹም ሰምተው። አበደ ብለዋልና ሊይዙት ወጡ። 22ከኢየሩሳሌም የወረዱ ጻፎችም። ብዔል ዜቡል አለበት፤ ደግሞ። በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል ብለው ተናገሩ። 23እነርሱንም ወደ እርሱ ጠርቶ በምሳሌ አላቸው። ሰይጣን ሰይጣንን ሊያወጣው እንዴት ይችላል? 24መንግሥትም እርስ በርስዋ ከተለያየች ያች መንግሥት ልትቆም አትችልም፤ 25ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ያ ቤት ሊቆም አይችልም። 26ሰይጣንም ራሱን ተቃውሞ ከተለያየ፥ መጨረሻ ይሆንበታል እንጂ ሊቆም አይችልም። 27ነገር ግን አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ ዕቃውን ሊበዘብዝ የሚችል የለም፥ ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል።

28እውነት እላችኋለሁ፥ ለሰው ልጆች ኃጢአት ሁሉ የሚሳደቡትም ስድብ ሁሉ ይሰረይላቸዋል፤ 29በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳደብ ሁሉ ግን የዘላለም ኃጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም። 30ርኵስ መንፈስ አለበት ይሉ ነበርና።

31እናቱና ወንድሞቹም መጡ በውጭም ቆመው ወደ እርሱ ልከው አስጠሩት። 32ብዙ ሰዎችም በዙሪያው ተቀምጠው ነበሩና። እነሆ፥ እናትህ ወንድሞችህም በውጭ ቆመው ይፈልጉሃል አሉት። 33መልሶም። እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነ ማን ናቸው? አላቸው። 34በዙሪያው ተቀምጠው ወደ ነበሩትም ተመለከተና። እነሆ እናቴ ወንድሞቼም። 35የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ ነው እኅቴም እናቴም አለ።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Mark 2
Top of Page
Top of Page