የሉቃስ ወንጌል 20
Amharic NT

1አንድ ቀንም ሕዝቡን በመቅደስ ሲያስተምር ወንጌልንም ሲሰብክላቸው፥ የካህናት አለቆችና ጻፎች ከሽማግሌዎች ጋር ወደ እርሱ ቀረቡና። 2እስኪ ንገረን፤ እነዚህን በምን ሥልጣን ታደርጋለህ ወይስ ይህን ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው? ብለው ተናገሩት። 3መልሶም። እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፥ እናንተም ንገሩኝ፤ 4የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? አላቸው። 5እርስ በርሳቸውም ሲነጋገሩ። ከሰማይ ብንል። ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ 6ከሰው ብንል ግን ሕዝቡ ሁሉ ይወግሩናል፤ ዮሐንስ ነቢይ እንደ ነበረ ሁሉ ያምኑ ነበርና አሉ። 7መልሰውም። ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም አሉት። 8ኢየሱስም። እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው።

9ይህንም ምሳሌ ለሕዝቡ ይላቸው ጀመር። አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ ለገበሬዎችም አከራይቶ ለብዙ ዘመን ወደ ሌላ አገር ሄደ። 10በጊዜውም ከወይኑ አትክልት ፍሬ እንዲሰጡት አንድ ባሪያ ወደ ገበሬዎች ላከ፤ ገበሬዎቹ ግን ደበደቡት ባዶውንም ሰደዱት። 11ጨምሮም ሌላውን ባሪያ ላከ፤ እነርሱም ያን ደግሞ ደበደቡት አዋርደውም ባዶውን ሰደዱት። 12ጨምሮም ሦስተኛውን ላከ፤ እነርሱም ይህን ደግሞ አቍሰለው አወጡት። 13የወይኑም አትክልት ጌታ። ምን ላድርግ? የምወደውን ልጄን እልካለሁ፤ ምናልባት እርሱን አይተው ያፍሩታል አለ። 14ገበሬዎቹ ግን አይተውት እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ። ወራሹ ይህ ነው፤ ርስቱ ለእኛ እንዲሆን ኑ እንግደለው አሉ። 15ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ ምን ያደርጋቸዋል? 16ይመጣል እነዚህንም ገበሬዎች ያጠፋል፥ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል። ይህንም በሰሙ ጊዜ። ይህስ አይሁን አሉ።

17እርሱ ግን ወደ እነርሱ ተመልክቶ። እንግዲህ። ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ ተብሎ የተጻፈው ይህ ምንድር ነው?

18በዚያም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይቀጠቀጣል፤ የሚወድቅበትን ሁሉ ግን ይፈጨዋል አለ።

19የካህናት አለቆችና ጻፎችም ይህን ምሳሌ በእነርሱ ላይ እንደ ተናገረ አውቀው በዚያች ሰዓት እጃቸውን ሊጭኑበት ፈለጉ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። 20ሲጠባበቁም ወደ ገዢ ግዛትና ሥልጣን አሳልፈው እንዲሰጡት ጻድቃን መስለው በቃሉ የሚያጠምዱትን ሸማቂዎች ሰደዱበት። 21ጠይቀውም። መምህር ሆይ፥ እውነትን እንድትናገርና እንድታስተምር ለሰው ፊትም እንዳታደላ እናውቃለን፥ በእውነት የእግዚአብሔርን መንገድ ታስተምራለህ እንጂ፤ 22ለቄሣር ግብር ልንሰጥ ተፈቅዶአልን? ወይስ አልተፈቀደም? አሉት። 23እርሱ ግን ተንኰላቸውንም ተመልክቶ። ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ? አንድ ዲናር አሳዩኝ፤ 24መልኩ ጽሕፈቱስ የማን ነው? አላቸው። መልሰውም። የቄሣር ነው አሉት። 25እርሱም። እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው። 26በሕዝቡም ፊት በቃሉ ሊያጠምዱት አልቻሉም በመልሱም እየተደነቁ ዝም አሉ።

27ትንሣኤ ሙታንንም የሚክዱ ከሰዱቃውያን አንዳንዶቹ ቀርበው ጠየቁት፥ 28እንዲህ ሲሉ። መምህር ሆይ፥ ሙሴ። ሚስት ያለችው የአንድ ሰው ወንድም ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፥ ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ ብሎ ጻፈልን። 29እንግዲያስ ሰባት ወንድማማች ነበሩ፤ የፊተኛውም ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ 30ሁለተኛውም አገባት፥ ሦስተኛውም፥ እንዲሁም ሰባቱ ደግሞ ልጅ ሳይተዉ ሞቱ። 31 32ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ደግሞ ሞተች። 33እንግዲህ ሰባቱ አግብተዋታልና ሴቲቱ በትንሣኤ ከእነርሱ ለማንኛቸው ሚስት ትሆናለች?

34ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። የዚህ ዓለም ልጆች ያገባሉ ይጋባሉም፥ 35ያን ዓለምና ከሙታን ትንሣኤ ሊያገኙ የሚገባቸው እነዚያ ግን አያገቡም አይጋቡምም፥ እንደ መላእክት ናቸውና፥ 36ሊሞቱም ወደ ፊት አይቻላቸውም፥ የትንሣኤም ልጆች ስለ ሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። 37ሙታን እንዲነሡ ግን ሙሴ ደግሞ በቍጥቋጦው ዘንድ ጌታን የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ በማለቱ አስታወቀ፤ 38ሁሉ ለእርሱ ሕያዋን ስለ ሆኑ፥ የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። 39ከጻፎችም አንዳንዶቹ መልሰው። መምህር ሆይ፥ መልካም ተናገርህ አሉት። 40ወደ ፊትም አንድ ነገር ስንኳ ሊጠይቁት አልደፈሩም።

41እንዲህም አላቸው። ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው እንዴት ይላሉ?

42ዳዊትም ራሱ በመዝሙራት መጽሐፍ። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ይላል።

43 44እንግዲህ ዳዊት። ጌታ ብሎ ይጠራዋል፥ እንዴትስ ልጁ ይሆናል?

45ሕዝቡም ሁሉ ሲሰሙ ደቀ መዛሙርቱን። 46ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞር ከሚፈልጉ፥ በገበያም ሰላምታ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥ በምሳም የከበሬታ ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠበቁ፤ 47የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ፥ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ አለ።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Luke 19
Top of Page
Top of Page