የማርቆስ ወንጌል 10
Amharic NT

1ከዚያም ተነሥቶ በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ ደግሞም ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ እንደ ልማዱም ደግሞ ያስተምራቸው ነበር።

2ፈሪሳውያንም ቀርበው። ሰው ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን? ብለው ሊፈትኑት ጠየቁት። 3እርሱ ግን መልሶ። ሙሴ ምን አዘዛችሁ? አላቸው። 4እነርሱም። ሙሴስ የፍችዋን ጽሕፈት ጽፎ እንዲፈታት ፈቀደ አሉ። 5ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ይህችን ትእዛዝ ጻፈላችሁ። 6ከፍጥረት መጀመሪያ ግን እግዚአብሔር ወንድና ሴት አደረጋቸው፤ 7ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ 8ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። 9እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው።

10በቤትም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር ጠየቁት። 11እርሱም። ሚስቱን ፈትቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ በእርስዋ ላይ ያመነዝራል፤ 12እርስዋም ባልዋን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች አላቸው።

13እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ያመጡአቸውን ገሠጹአቸው። 14ኢየሱስ ግን አይቶ ተቈጣና። ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ አትከልክሉአቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ናትና። 15እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም አላቸው። 16አቀፋቸውም እጁንም ጭኖ ባረካቸው።

17እርሱም በመንገድ ሲወጣ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ ተንበረከከለትና። ቸር መምህር ሆይ፥ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው። 18ኢየሱስም። ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። 19ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አታታልል፥ አባትህንና እናትህን አክብር አለው። 20እርሱም መልሶ። መምህር ሆይ፥ ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ አለው። 21ኢየሱስም ወደ እርሱ ተመልክቶ ወደደውና። አንድ ነገር ጐደለህ፤ ሂድ፥ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መስቀሉንም ተሸክመህ ና፥ ተከተለኝ አለው። 22ነገር ግን ስለዚህ ነገር ፊቱ ጠቈረ፥ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነም ሄደ።

23ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን። ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል አላቸው። 24ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ። ኢየሱስም ደግሞ መልሶ። ልጆች ሆይ፥ በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው። 25ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል አላቸው። 26እነርሱም ያለ መጠን ተገረሙና እርስ በርሳቸው። እንግዲያ ማን ሊድን ይችላል? ተባባሉ። 27ኢየሱስም ተመለከታቸውና። ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ እንጂ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላልና አለ።

28ጴጥሮስም። እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ ይለው ጀመር። 29ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፥ 30አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም። 31ግን ብዙ ፊተኞች ኋለኞች ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ።

32ወደ ኢየሩሳሌምም ሊወጡ በመንገድ ነበሩ፥ ኢየሱስም ይቀድማቸው ነበርና ተደነቁ፤ የተከተሉትም ይፈሩ ነበር። ደግሞም አሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ አቅርቦ ይደርስበት ዘንድ ያለውን ይነግራቸው ጀመር። 33እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች አልፎ ይሰጣል፥ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፥ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል፥ 34ይዘብቱበትማል ይተፉበትማል ይገርፉትማል ይገድሉትማል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል አላቸው።

35የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ወደ እርሱ ቀርበው። መምህር ሆይ፥ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንወዳለን አሉት። 36እርሱም። ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው። 37እነርሱም። በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝ አንዳችንም በግራህ መቀመጥን ስጠን አሉት። 38ኢየሱስ ግን። የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ፥ እኔ የምጠመቀውንስ ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን? አላቸው። 39እነርሱም። እንችላለን አሉት። ኢየሱስም። እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፥ እኔ የምጠመቀውንም ጥምቀት ትጠመቃላችሁ፤ 40በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን ለተዘጋጀላቸው ነው እንጂ የምሰጥ እኔ አይደለሁም አላቸው።

41አሥሩም ሰምተው በያዕቆብና በዮሐንስ ይቈጡ ጀመር። 42ኢየሱስም ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው። የአሕዛብ አለቆች ተብሎ የምታስቡት እንዲገዙአቸው ታላላቆቻቸውም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ። 43በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥ 44ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤ 45እንዲሁ የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።

46ወደ ኢያሪኮም መጡ። ከደቀ መዛሙርቱና ከብዙ ሕዝብ ጋር ከኢያሪኮ ሲወጣ የጤሜዎስ ልጅ ዕውሩ በርጤሜዎስ እየለመነ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ነበር። 47የናዝሬቱ ኢየሱስም እንደ ሆነ በሰማ ጊዜ። የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ እያለ ይጮኽ ጀመር። 48ብዙዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን። የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ እያለ አብዝቶ ጮኸ። 49ኢየሱስም ቆመና። ጥሩት አለ። ዕውሩንም። አይዞህ፥ ተነሣ፥ ይጠራሃል ብለው ጠሩት። 50እርሱም እየዘለለ ተነሣና ልብሱን ጥሎ ወደ ኢየሱስ መጣ። 51ኢየሱስም መልሶ። ምን ላደርግልህ ትወዳለህ? አለው። ዕውሩም። መምህር ሆይ፥ አይ ዘንድ አለው። 52ኢየሱስም። ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው። ወዲያውም አየ በመንገድም ተከተለው።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Mark 9
Top of Page
Top of Page